የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች ዛሬ በዓለም ደረጃ ለሚደመጡት መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች መነሻ እንደሆኑ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል፡፡ የዓለም የሙዚቃ ጠበብት የሚባሉት ሞዛርት እና ቬትሆቨንን ጨምሮ ሌሎችም በየ ዘመናቱ የተፈጠሩት ሊቃውንት መነሻቸው የኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ የዜማ ቅመራ እንደሆነ አሁንም የታሪክ ድርሳናት እማኝ ይሆናሉ፡፡ ይህ ሁነት ኢትዮጵያ በቅድመ ሥልጣኔዋ በጥበቡም ዘርፍ ቀዳሚ መሆኗን ያሳያል፡፡
ሙዚቃ የዓለም መነጋገሪያ ቋንቋ ነው፤ ሙዚቃ የመንፈስ ምግብ ነው፤ሙዚቃ የስሜት ነፀብራቅ ነው... ሲባል እንሰማለን፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ሙዚቃ ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው በተለያዩ ምሁራን የተጠኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በፅንስ ደረጃ ያለ ሕፃን ሙዚቃን ለይቶ እንደሚነቃቃ ተፅፏል፡፡ በእንስሳት እና በዕፅዋት ላይ ሙዚቃ የሚፈጥረው ስሜት ስለመኖሩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ በሌሎች ያደጉ አገራት ሙዚቃ አንዱ የህክምና ጥበብ ሆኖ ፈውስን መስጠት ከጀመረ ዘመናት ተቆጥሯል፡፡ ዛሬም ጥበቡ የየ አገራቱን ዜጎች ከክፉ ደዌ እየታደጋቸው መሆኑ እየተሰማ ነው፡፡
ሙዚቃ ለህሙማን ስቃያቸውን እያስረሳ ተስፋን የሚሰጣቸው መሆኑ የታመነው እ.አ.አ1789 አካባቢ ነው፡፡ ጉዳዩ «ኮሎምቢያ» በተሰኘ መጽሔት ከወጣ ወዲህ ትኩረት አግኝቶ በየ ዘመናቱ ጥበቡ እያደገ መጣ፡፡ በተለይ የአንደኛው እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንዱ የህክምና ጥበብ ሆኖ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ወቅት በአሜሪካን አገር በጦርነት አካላዊ እና አዕምሯዊ ጉዳት ደርሶባቸው በየ ካምፑ እና ሆስፒታሎች የሚያገግሙ ህሙማንን ሙያዊ የሙዚቃ እውቀት ያላቸው እና ሌሎች በጎ ፈቃድ ያላቸው የልምድ ሙዚቀኞች ሙዚቃን እንዲጫወ ቱላቸው በመደረጉ ከፍተኛ የመነቃቃትና የመሻል ለውጥ እንዳሳዩ ታውቋል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሙዚቃ እንደ አንድ የህክምና ጥበብ ተቆጥሮ ራሱን የቻለ ሣይንሳዊ ትምህርት እንዲኖረው ሆነ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ኮሌጆች በዘርፉ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቶ እ.አ.አ በ1944 የመጀመሪያው ሙዚቃዊ ህክምና ትምህርት በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ተከፍቶ የህክምና ጥበቡ ሣይንሳዊ መልክ ያዘ፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና የነበረው ኢ.ታየር ጋስቶን የተባለ አሜሪካዊ የሙዚቃ ጠበብት ሙዚቃ አንዱ የህክምና ዘርፍ ሆኖ እንዲሠራበት ባደረገው አስተዋፅኦ የሙዚቃ ህክምና አባት እስከመባል ደርሷል፡፡ በዚህ ረገድ ቀዳሚ የሆነችው አሜሪካ ብትሆንም ዛሬ መላው አውሮፓና ሌሎች ያደጉ አገራት ሣይንሳዊ ጥበቡን እየተጠቀሙበት እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሜሪካን ዛሬ በዚሁ የህክምና ጥበብ ከ 5 ሺ በላይ ሙያተኞች ህጋዊ ፈቃድ አግኝተው ህሙማንን የሚያገለግሉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከ30 በላይ አገራት ውስጥ የሙዚቃ ህክምና ሙያተኞች ማህበር በአባላት እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንዳንድ ዘመናዊ የህክምና ጥበብን ማግኘት የሚቻለው አገራት ካላቸው የዕድገትና ሥልጣኔ ደረጃ አንፃር ቢሆንም ምንነታቸውንና ጠቀሜታቸውን ማወቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር ሙዚቃዊ ህክምና በአገራችን እስከ ምን ድረስ ይታወቃል? ጠቀሜታውስ ምንድነው? ሌሎች አገራት የደረሱበትስ ደረጃ ምን ይመስላል የሚሉትን ጥያቄዎች የሚመልስ አንድ መድረክ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሄዶ ነበር፡፡
በርካታ የሙዚቃ ጠበብትና የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የመንግሥት አካላት በተገኙበት ጥቅምት 27/2008 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ከፍታ ሲኒማ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ፤ ስለ ሙዚቃዊ ህክምና ምንነትና ጠቀሜታ የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሑፍም ቀርቧል፡፡ ይህንን ጥናት ያቀረቡት ዶክተር መልካሙ መዓዛ ሲሆኑ፤ በጥናቱ ላይ ተሳታፊዎች የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በጥቅሉ ጥናቱ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ መቅረቡ የሚበረታታ ሆኖ፤ የህክምና ጥበቡን በአገራችን ለመጀመር የሚያስችል የመጀመሪያ ማሳያ መሆኑም ተነግሯል፡፡
ዶክተር መልካሙ አጠቃላይ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ደግሞ በተሳትፎ ሙዚቃ ይጫወታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ባላቸው የሙዚቃ ፍቅርና ተሰጥኦ ባደጉ አገራት በስፋት የተለመደውን የሙዚቃ ህክምና(ቴራፒ) አገልግሎት በአገራችን ለማስተዋቅና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሠፊ ጥናትና ዳሰሳ እያደረጉ ነው፡፡
ዶክተር መልካሙ ከአሁን ቀደም «ዲፕ አቢሲኒያ» የተሰኘ አልበም ሠርተው ያሰራጩ ሲሆን፤ የዚሁ አልበም ድምፅ ቀረፃውንና የመሣሪያ ጨዋታውንና ቅንብሩን ራሳቸው እንዳዘጋጁት በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በዚሁ ዕለትም «ትራይባል ማጂክ» የሚል ስያሜ ያለውን ሁለተኛ የሙዚቃ አልበማቸውን አስመርቀዋል፡፡ በዚሁ ጊዜም በነጩ አገር ልብስ ደምቀው ከዚሁ አልበም ውስጥ የመረጡትን በመድረኩ ላይ በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ኦርጋንና ኮምፒዩተር ታግዘው ለታዳሚው ያስደመጡት የሙዚቃ ቅንብራቸው ለራሳቸው ለዶክተር መልካሙም ደስታ ነው የፈጠረላቸው ፡፡
ዶክተር መልካሙ በመድረኩ ስለ ጥናታዊ ጽሑፋቸው አጠቃላይ ይዘትና መልዕክት የገለጹትን በማስቀደም፤ ሙዚቃዊ ህክምና ለአገራችን ስለሚኖረው ጠቀሜታ፣ አልበማቸውና የመሳሰሉት ጉዳዮች የሰጡንን ማብራሪያ እንደሚከተለው እናስነብባለን፡፡
ዶክተር መልካሙ በዚሁ በሣይንስ በተደገፈ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ስለ ሙዚቃዊ ህክምና ታሪካዊ አመጣጥና ዛሬ ያለበትን ደረጃ አሳይተዋል፡፡ ባደጉት አገራት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ትምህርቱ የሚሰጥና ራሱን የቻለ ዩኒቨርሲቲም እንደተቋቋመ አሳይተዋል፡፡ መንግሥታት ለሙያው በሰጡት ልዩ ትኩረትም በተለይ በአሜሪካ እስከ ፒ.ኤች.ዲ ድረስ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ እየታመነበት፣ ውጤት እየታየበት፣ እየተወደደና እየተለመደ የመጣ የህክምና ጥበብ መሆኑንም በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡
በምስልና ድምፅ ያስደገፉት ይህ ጥናታቸው በጣም የደካከሙ፣ መንቀሳቀስና መናገር ያልቻሉ ህሙማን ቀስ በቀስ ሙዚቃ ሲሰሙ እንዴት ያለ የመንፈስ ደስታና የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ እንደቻሉ አሳይተዋል፡፡ ሙዚቃ በማንኛውም የሰው ልጅ ህዋስ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ውስጥን የማነቃቃት ተፈጥሯዊ ኃይል እንዳለው የሚናገሩት ዶክተር መልካሙ እንኳንስ ለአዋቂ በሆድ ውስጥ ላለው ፅንስም መልዕክት እንዳለው ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር መልካሙ ማብራሪያ፤ የሰው ልጅ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ በሽታዎች ሊያጠቁት ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በመድሃኒት ብቻ ህክምና ከመስጠት ይልቅ ሙዚቃንም ተጓዳኝ መፍትሔ ሰጪ ህክምና ማድረጉ እየታመነበት ነው፡፡ ሙዚቃዊ ህክምና በነርቭ፣ በአዕምሮ ዝግመት፣ በጭንቀት፣ በአካል ጉዳት፣ በራስ መሳት እና በሌሎችም ህመም ውስጥ ላሉ የሰው ልጆች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተረጋግጧል፡፡ ይህን ህክምና ያደጉ አገራት በርትተው እየተጠቀሙበት በመሆኑ ዜጎቻቸው አማራጩን ህክምና እየወደዱት ነው፡፡ ሙዚቃው ምን ዓይነት፣ ለማን፣ መቼ እና እንዴት ይሰጥ የሚለው እየተለየ ሣይንሳዊ በሆነ መልኩ የፈውስ ህክምና ላይ እየዋለ ነው፡፡ ከዕድሜ ከባህል ከሃይማኖትና የራስ ማንነት አንፃር እየተለየ የሚሰጠው የሙዚቃ ማስደመጥ ህክምና ህሙማንን ቀስ በቀስ የማዳንና ወደ ቀደሞ ማንነታቸው እንዲመለሱ እያስቻለ መሆኑንም ነው የሚገልጹት፡፡
ይህ የህክምና ጥበብ በሀገራችንም ሊሰጥ የሚያስችል ሠፊ ዕድል አለ፡፡ ከሁን ከካን የዕድገት ደረጃ አኳያ የህክምና ጥበቡ በዩኒቨርሲቲ ይሰጥ የሚል ሃሳብ ማቅረብ ቢያዳግትም፤ ካሉን የተለያዩ ባህላዊ፣ መንፈሳዊና ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ብዛት አንፃር ህሙማንን በየ ሆስፒታሉ፣ በየ ቤቱ እና ለሙዚቃ መስማት ምቹ በሆኑበት ቦታዎች ሁሉ መስጠት ይቻላል ባይ ናቸው፡፡
ሙዚቃዊ ህክምና ጥቅም በሀገራችን በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ከመታወቁ በዘለለ ከአሁን ቀደም ምንም ዓይነት ጥናት እንዳልተደረገበት የሚናገሩት ዶክተር መልካሙ፤ ነገ የዚህ ጥበብ ተቋዳሽ መሆን ለማይቀርልን ዛሬ «ሀ»ብሎ መጀመሩ እንደሚበጅ ይናገራሉ፡፡ በዚህም እርሳቸው ባላቸው እውቀትና ክህሎት ለማገዝ ሙሉ ፈቃድ እንዳላቸውም ይገልጻሉ፡፡
ለህብረተሰቡ ስለ ህክምናው ግንዛቤን ማስጨበጥ ቀዳሚ ሥራ ሆኖ መንግሥት ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ ቢሆን መልካም ጅምር እንደሚታይ የሚናገሩት ዶክተር መልካሙ፤ በዚህ ረገድ የሙዚቃ ባለሙያዎችና የህክምና ባለሙያዎች የጋራ ግንዛቤና ስምምነት ሊያደርጉ እንደሚገባም ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ዛሬ በዘርፉ ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ማየት ቀዳሚ ሊሆን እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ የእርሳቸውም ጥናታዊ ጽሑፉ መነሻ ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡
ቅዱስ ዳዊት በበገናው በመጫወት ንጉሥ ሳኦልን ከነበረበት ክፉ መንፈስ እንዳዳነው በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀሱን በምሳሌ የሚነገሩት ዶክተር መልካሙ፤ ይህ አንዱ ለሙዚቃ ህክምና መነሻችን ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ በባህላዊና መንፈሳዊ ጥቅም የምንገለገልበት የራሳችን የሆነ በገና ለአርምሞ፣ ለጥሞናና ለመንፈስ ማነቃቂያ ከፍተኛ ጥቅም አለው ብለው እንደሚያምኑም ይናገራሉ፡፡ ሌሎችን ባህላዊና መንፈሳዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻች ሣይንሳዊ እውቀት ባላቸው ሙያተኞች ጥቅም ላይ ቢውሉ ህሙማንን ለማጽናናት፣ ለማነቃቃት ብሎም ለመፈወስ አቅም እንዳላቸው የሚያመላክት ተስፋ እንዳለ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ግን በጥናት መረጋገጥ እንደሚገባውም በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡
ዶክተር መልካሙ በራሳቸው ስቱዲዮ በኦርጋንና በኮምፒዩተር ብቻ በመታገዝ ባህላዊውን ከዘመናዊው ሙዚቃ ጋር በማቀነባበር ያሳተሙት አልበም የራሳቸውንና የሌሎችን ድምፅ ተጠቅመዋል፡፡ በአልበሙ ተስፋን፣ መጽናናትን፣ ደስታን፣ ኀዘንን፣ መከፋትን፣ መበርታትንና ሌሎችንም በሰው ልጆች ላይ የሚፈራረቁ የስሜት ሁነቶችን የሚዳስሱ መልዕክቶች የተላለፉበት ነው፡፡ ባህላዊና ህዝባዊ ዘፈኖች ያሉበትና በልዩ ሙዚቃዊ ቅንብር የተሠራው አልበም ውስጥ ድምፃቸው የሚሰማው ዶክተር መልካሙ፤ በአልበሙ ውስጥ የሚሰሙት አንዳንድ ግጥሞች የእርሳቸው ናቸው፡፡
ከልጅነታቸው ጀምሮ ሙዚቃን የመስማት ፍላጎት ቢኖራቸውም ቀስ በቀስ በግላቸው እንዳዳበሩት፣ ሙዚቃ በሕይወታቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ፤ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት ላይ እያሉም ሆነ ከዚያ ወጥተው በህክምናው ዘርፍ ሲሰማሩ ሙዚቃ መስማትና በተቻላቸው አቅም ከመጫወት ታቅበው አያውቁም፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን ሙዚቃ ለህክምናም እንደሚውል ካነበቡት በመረዳታቸው በጉዳዩ ልዩ ትኩረት እየሰጡ ነው፡፡ በዚህም ጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ እቅዳቸውም ሠፊ ነው፡፡
አዲስ ያወጡት አልበም ከሙዚቃ ህክምና ጋር የተያያዘ ጥቅም እንዳለው ለተጠየቁት ሲመልሱ፤ «ለግላዊ ስሜቴ መወጫ ብዬ ያወጣሁት እንጂ አልበሜ ላይ የሚደመጡት ሙዚቃዎች ለፈውስ ህክምና ይውላሉ የሚል እምነትም ሆነ ሃሳቡ የለኝም» ነው ያሉት፡፡ ጥናት ከተደረገ ግን የእርሳቸውም ሆነ የሌሎች ሙዚቀኞች ሙዚቃ ለህሙማን በተለያየ መልኩ የሚጠቅምበት መንገድ ሊኖር እንደሚችል ግምት አላቸው፡፡
በሙያቸው የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ሀኪም ሲሆኑ በማህበረሰባዊ ጤና ሣይንስም የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ዶክተር መልካሙ ይህ መሆኑ ከጤናም ሆነ ከሰው ልጆች ፍላጎትና አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ግንዛቤያቸው ሠፊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህም ለሚያደርጉት ጥናት እንደሚጠቅማቸው ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ዝዋይ በሚገኘው ሼር ኢትዮጵያ በተሰኘ ሆስፒታል ውስጥ በሙያቸው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
ሣይንሳዊ ጥበብ ከሰው ልጅ የአዕምሮ ልህቀት ጋር አብሮ እያደገ፤ በየ ዘመናቱ ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሆኑ ግኝቶች መፈልሰፋቸው አልቀረም፡፡ በዘመናችን በተለይም ለሀገራችን እንደ አንድ ግኝት የሚታሰበው ይህ ሙዚቃዊ ህክምና በሌሎች አገራት ግን ተፈላጊነቱ እየጎላ ጥበቡም እያደገ ነው፡፡ እዚህ በእኛ አገር ይህ ግኝት ከባህል ከሃይማኖትና እምነት ሥርዓት ጋር «እንዴት ጥቅም ላይ ይዋል?» የሚለው ሌላው ቀዳሚ ጥናት ሆኗል፤ ጥቅሙን ግን ከሌሎች አገራት ተሞክሮ መቅሰሙ አይከፋም እንላለን፡፡ በግርምት «ሙዚቃንም ለህከምና?» የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ ግን ከላይ የተጠቀሱ እውነታዎች ምላሽ ይሰጣሉ ብለን እናስባለን፡፡
ደረጀ ትዕዛዙ
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/society/item/4505-2015-11-30-13-41-12
No comments:
Post a Comment